ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ በኢትዮጵያ የጀርመን ምክትል አምባሳደር ፈርዲናንድ ፎን ቫሄን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ። ምክትል አምባሳደሩ የአዲስ ዓመት መልካም ምኞታቸውን ለቅዱስ ፓትርያርኩ ገልጸዋል ።
መስከረም ፭ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ምብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ በኢትዮጵያ የጀርመን ምክትል አምባሳደር ፈርዲናንድ ፎን ቫሄን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው በማነጋገር ውይይት አድርገዋል።
አዲስ አበባ የሚገኘው የጀርመን ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ፈርዲናንድ ፎን ቫሄ መስከረም ፭ ቀን ፳፻፲፱ ዓ.ም ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ እንኳን አደረስዎ ለማለትና እና መልካም ምኞታቸውን ለመግለጽ ነው በጽርሐ መንበረ ፓትርያርኩ የተገኙት፡፡
በዕለቱም ከቅዱስነታቸው ጋር ሰፊ ውይይት ያደረጉ ሲሆን ምክትል አምባሳደሩ በዚህም በጣም ደስተኛ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ቅዱስ ፓትሪያርኩ ይህንን የመገናኘት እድል ስለሰጡኝና በብዙ ርዕሶች ላይ ግልጽ ውይይት በማድረጋችን በጣም ደስተኛ ነኝ ያሉት ምክትል አምባሳደር በውይይታቸው ወቅትም በጀርመን የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክሳውያን መኖራቸውን እንደገለጹላቸውም አንስተዋል፡፡
ይህንን እኔም በልምድ ያየሁት ነው ያሉት አምባሳደሩ አሁን በጀርመን የሚኖሩ በርካታ ኢትዮጵያውያን አማኞች አሉ ብለዋል፡፡እምነታቸውን ለማስቀጠልም እንደ ሥርዓታቸው የሚያመልኩበት ቦታና ማህበረሰብ እንዲኖራቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ካህናት አብረዋቸው አሉ ፤ይህም በጣም አስፈላጊ ይመስለኛል ብለዋል ። በተጨማሪም እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ ጀርመናውያን ክርስቲያኖች መኖራቸውን ጠቅሰው ከቅዱስነታቸው ጋር እንደተወያየነው በዚህ ሳምንት መጨረሻ እዚሁ አዲስ አበባ የሚገኘውን የጀርመን ፕሮቴስታንት ቤተክርስቲያን 60ኛ ዓመት እናከብራለንም ብለዋል።
አያይዘውም ቅዱስ ፓትርያርኩን ሳገኝና ስወያይ የመጀመሪያ ጊዜዬ አይደለም ያሉ ሲሆን ለዚህም ቅዱስነታቸውን አመስግነዋል፡፡
የሁላችንም እምነት ሕይወታችንን በጣም የሚወስን ነገር እንደሆነ አምናለሁ ያሉት ምክትል አምባሳደሩ በአዲስ አበባ ዙሪያ ስንቀሳቀስ፣ ብዙ ሰዎች ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ፣ ጾም ሲጾሙ፣ መስቀልንና ጥምቀትን ሲያከብሩ አያለሁ፤ከዚህም የተነሳ በዚህች ሀገር እምነት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ እረዳለሁ ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳውያን አማኞች ለእምነታቸው ያላቸውን ስፍራ አድንቀዋል። በመሆኑም እኔ እንደ ዲፕሎማት ከአማኞች መሪዎች ጋር መገናኘትና የዚችን ቤተክርስቲያን አስፈላጊነት መረደት አስፈላጊ ሆኖ ተሰምቶኛልም ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ለመላው የእምነቱ ተከታይ መልካም ምእመናን ምኞታቸውን ገልጠው በቀጣይ የሚመጣውን የመስቀል በዓልም አብሮ ለማክበር እናፍቃለሁም ሲሉ አጠቃለዋል፡፡
በውይይቱ ፍጻሜም የመልካም ምኞት መግለጫ ስጦታ ለቅዱስነታቸው ያበረከቱ ሲሆን ቅዱስነታቸውም በተመሳሳይ ለምክትል አምባሳደር ሰጦታ አበርክተውላቸዋል፡፡
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/
