ከአሜሪካ የተመለሱ 17 የኢትዮጵያ መንፈሳዊ የብራና መጻሕፍት ለሰባት ተቋማት ተከፋፈሉ።
በመቅደላ ጦርነት የተዘረፈውን ወንጌል ጨረታ ለማስቆም ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ተገልጿል።መስከረም 5 ቀን 2019 ዓ.ም
በኢትዮጵያ የቅርስ ባለስልጣን አዳራሽ በተካሄደ ደማቅ ሥነሥርዓት፣ ከአሜሪካ የተመለሱ 17 ውድ የኢትዮጵያ መንፈሳዊ የብራና መጻሕፍት ለሰባት የኢትዮጵያ ተቋማት በስጦታ ተላለፉ። በዚህ ታሪካዊ የርክክብ መርሐ-ግብር ላይ የባለስልጣኑ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከአሜሪካ የመጡ የአጥኝዎች ቡድን አባላት፣ ታዋቂ አርቲስቶችና የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ የቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረ/ፕ አበባው አያሌው ባደረጉት ንግግር፣ እነዚህ የሀገር ባሕልና ታሪክ መገለጫ የሆኑ ቅርሶች ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይም ከ1970ዎቹ ጀምሮ በሕገ-ወጥ መንገድና በምስጢር ከሀገራችን ወጥተው የቆዩ መሆናቸውን አስታውሰዋል። ቅርሶቹን ወደ እናት ሀገራቸው ለመመለስ የተደረገው ጥረት ውጤት ማምጣቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ ለተቋማቱ መተላለፋቸው ለጥናትና ምርምር እንዲሁም ቅርሶቹን ጠብቆ ለትውልድ ለማቆየት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አክለው ገልጸዋል።
የተመለሱት 17ቱ የብራና መጻሕፍት እንደየይዘታቸውና ለጥናትና ምርምር ካላቸው ጠቀሜታ አንጻር ለሚከተሉት ሰባት የሀገሪቱ ተቋማት ተከፋፍለዋል፦
-ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጠቅላይ ቤተክህነት፦ 7 መጻሕፍት
-ለኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት (ወመዘክር)፦ 2 መጻሕፍት
-ለኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን፦ 2 መጻሕፍት
-ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም (IES)፦ 2 መጻሕፍት
-ለማኅበረ ቅዱስ 2 መጻሕፍት
– ለኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን መካነ ኢየሱስ እና ለኃይሌ ሚነስ አካዳሚ የቀሩት መጻሕፍት በስጦታ አንዳንድ መጻሕፍት ተበርክቶላቸዋል ።
በተለይም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከተመለሱት መጻሕፍት መካከል አርባዕቱ ወንጌል፣ የዓመቱ መጀመሪያ አጋማሽ ስንክሳር እና ውዳሴ ማርያም እንደሚገኙበት በሥነሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።
በሌላ በኩል፣ በ1860 ዓ.ም. በመቅደላ ጦርነት ወቅት በእንግሊዝ ጦር የተዘረፈውንና በአጼ ቴዎድሮስ እጅ የነበረን ውድ የኢትዮጵያ የወንጌል የብራና መጽሐፍ፣ በአሁኑ ወቅት በአቡ ዳቢ ለጨረታ ያቀረበውን የኦስትሪያውን ኢንሊብሪስ (Inlibris Gilhofer Nfg) ድርጅት ሽያጭ ለማስቆም ሰፊ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እየተደረገ መሆኑ በዕለቱ ተጠቁሟል።
ድርጅቱ ለዚህ ታሪካዊ ቅርስ 250 ሺህ ዩሮ (በኢትዮጵያ ብር ወደ 47 ሚሊዮን ገደማ) የመነሻ ዋጋ ጠይቆ ለሽያጭ አቅርቦታል። ይህንን ሕገ-ወጥ የቅርስ ሽያጭ ሙሉ በሙሉ ለማስቆም እና ቅርሱን ወደ ሀገሩ ለመመለስ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን፣ የቱሪዝም ሚኒስቴር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በጋራ በመሆን የሕግና የዲፕሎማሲ ሂደቶችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ተገልጿል። ይህ ታሪካዊ የቅርስ መመለስ መርሐ-ግብር በሕገ-ወጥ መንገድ የጠፉና የተዘረፉ ሌሎች የሀገራችን ቅርሶችን ለማስመለስ ለሚደረገው አገራዊ ጥረት ትልቅ ማበረታቻና ማሳያ መሆኑ ተመልክቷል።
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/
