በበአታ ለማርያም ገዳም የ2.5 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ቡራኬ ተቀመጠ።

መስከረም ፬/፳፻፲፱ ዓ/ም የአ/አ/ሀገረ ስብከት ሚዲያ
በበአታ ለማርያም ገዳም የ2.5 ቢሊዮን ብር ፕሮጀክት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ቡራኬ ተቀመጠ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በተለይም ከ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መግቢያ ወዲህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉ ጥንታውያት ገዳማትና የአብነት ትምህርት ቤቶች መካከል በቀዳሚነት ከሚጠቀሱት የዳግማዊ አጼ ምኒልክ መታሰቢያ ታዕካ ነገሥት በአታ ለማርያም ገዳም አንዷ ነች!
በተለይም 93 ዓመታትን ያስቆጠረው የአብነት ትምህርት ቤትና የአረጋውያን መርጃና የዕጓለ ማውታ ማሳደጊያ ተቋማት ታሪካቸውን በሰው ልብ ላይ በደማቅ ቀለም የጻፉት ዋነኞቹ ናቸው።
የገዳሙ አስተዳዳሪ ሊቀ ሊቃውንት አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ እንደገለጹት በዓታ ለማርያም ገዳምና አብነት ትምህትር ቤት ከ28 በላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የተገኙበት፤ በሀገረ ውስጥና በውጭ ሀገራት እናት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያችንን የሚያገለግሉ ሊቃውንት የተገኙበት ባለውለት ቅዱስ ቦታ ነው በማለት ገልጸዋል።
ለዚህም በገዳሙ ትምህርት ቤት የሚሰጡት 8ቱ ጉባኤያት ማለትም የንባብ፣ የዜማ -ድጓ፣ የቅኔ ፣ የአቋቋም ፣ የቅዳሴ ፣ የመጻሕፍተ ብሉያት ትርጓሜ፣ የመጻሕፍተ ሐዲሳት ትርጓሜ እና የመጻሕፍተ ሊቃውንት ትርጓሜ ጉባኤ ቤቶችን ሰው በእውቀት የሚሠራባቸውን፣ በሕይወት የሚበስልባቸውና በጸጋ የሚጎበኝባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በገዳሙ ዘመናቸውን የሰጡ መምህራንና አገልጋዮች በእርጅና ጊዜያቸው የሚረዱበት እንዲሁም ወላጆቻቸው የሞቱባቸው ሕጻናት የሚያድጉበት ለ93 ዓመታት አገልግሎት የሰጠና በቅርቡ በኮሪደር ልማት አማካኝነት የፈረሰ የሰው የልብ ኀዘንን የሚደገፍበት፣ ማናለኝና ምን ላገኝ ከሚል ተስፋ መቁረት የሚተርፉበት የመርጃ ማእከል በዚሁ ቦታ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ይህን እንጂ በዚህ ቦታ የተደረገው ነገር ቢኖር ያለውን በተቻለው አቅም መጠበቅ እንጂ በቀጣይ ስለሚያስፈልገውና ለትውልዱ ስለሚገባው ዘመኑን የዋጀ ታሪካዊ ሥራ በብዙ መልኩ ከሐሳብ የዘለለ ተግባራዊ ሥራ እንዳልታየበት አስታውሰዋል።
ስለሆነም እውነተኛ መቆርቆር ታሪክ ያሠራል፣ ተገቢ ቁጭት ዓላማን ያስጠብቃል ነውና የትናንትን ታሪክ መልሶ ወደ ክብሩ ለመመለስና አገልገሎቱን ለማስፋት ይቻል ዘንድ #በ2.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት የገዳሙ ፕሮጀክት ግንባታ ለማስጀመር በትናትናው ዕለት የመሠረት ድንጋይ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ቡራኬ መቀመጡ በእጅጉ እንዳስደሰታቸውን ሊቀ ሊቃውንት አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ በ9357 ካሬ ሜትር የሚያርፍ ሲሆን በውስጡም ለመምህራንና ቀሳውስት ማሰልጠኛ አብነት ትምህርት ቤት ፣ ለመምህራንና ደቀመዛሙርት ማረፊያ ፣ ለአረጋውያን መርጃና ለዕጓለ ማውታ ማሳደጊያ ፣ ለገዳሙ ጽፈት ቤት አገልግሎት፣ ለሰብከተ ወንጌል ማስፋፊያ ፣ ለሰንበት ትምህርት ቤት ማጠናከሪያ የሚሆኑ የተለያዩ ሕንጻዎች እንደሚኖሩት ተጠቁሟል።
ፕሮጆክቱ ሲጠናቀቅም ከመላው ኢትዮጵያ ለትምህርት የሚመጡ ደቀ መዛሙርት የቅበላ አቅሙን በእጅጉ ያሳድገዋል፤ ከ93 ዓመታት በላይ ያገለገለውንና በኮሪደሩ ምክንያት የፈረሰውን የአረጋውያን መርጃና የዕጓለ ማውታ ማሳደጊያ ተቋምን መልሶ አገልግሎቱን ለመስጦት ያስችላል፤ እንዲሁም ትምህርቱን ዘመኑን በዋጀ መልኩ በበይነ መረብ ጭምር ከመስጠት ባለፈ ደቀ መዛሙርቱን የዓለማዊ ትምህርትን ጎን ለጎን የሚማሩበትን ሁኔታ የሚመቻችበት መደላድልን በእጅጉ ይፈጥራል ተብሏል።
በመርሐ ግብር ላይ አባታዊ መልእክታቸውን ያስተላላፉት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ገዳሟ ታሪክ የተሠራባት ለሀገርም ቤተ ክርስቲያንም ዋጋ የከፈሉ ሰዎች የተገኙባት ባለክቡር ታሪክ ባለቤት ብትሆንም አባቶችን ከሠሩት ድንቅ ሥራ ውጭ እንደሚፈለገው መጠን ተሠርቷል ለማለት አያስደፍርም ብለዋል። ይሁንንና ጊዜ ደርሶ ሰው ተገኝቶ ይህን የመሰለ ለታሪክ የሚነገር ድንቅ የፕሮጀክት መሠረት ድንጋይ በመጣሉ በእጅጉ ደስታውን ገልጸዋል። ለዚህም ሊቀ ሊቃውንት አባ ተክለ ሃይማኖት ወልዱና አብረዋቸው የሚወጡ የሚወርዱ አገልጋዮችና ደጋግ ምእመናን ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።
ከሰውም ሰው በቦታም ቦታ አለውና ይህች ገዳም ታሪኳ ሰፊ፣ አገልግሎቷ ብዙና አበርክቶቷ የሚደነቅ መሆኑ የሚታወቅ ነው። በተለይም በአብነት ትምህርቱ ላይ እየተሠራ የመጣው ቤተ ክርስቲያናዊ ሥራ ሲታወስ አብነቱ ቤተ ክርስቲያን በምን ያህሉ እንደጠቀማት ማሳያ ነው ብለዋል።
የአብነት ትምህርት ቤተ ክርስቲያንን ለትውልድ የሚያሻግር ድልድይ ነው ያሉት ብፁዕነታቸው የገዳሙን አብነት ትምህርት ቤትን መደገፍ የማይደርቅ ምንጭን እንደመጠበቅ ነው። ስለሆነም በዚህ መልካም ተግባር ቅዱስ ሲኖዶስም ሆነ መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲሁም ብፁዓን አባቶች በቀዳሚነት እንደሚያግዙና ከጎን እንደሚቆሙ ገልጸዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ ፣ ብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ዲዮስቆሮስ ሊቀ ጳጳስ ፣መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ መልአከ ምሕረት አባ ገብረ እግዚአብሔር ታደለ የአራዳ ጉሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣ መልአከ ፀሐይ በቀለ ተሰማ የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ፣ ሊቀ ሊቃውንት አባተ ተክለ ሃይማኖት ወልዱ የገዳሙ አስተዳዳሪ፣ የገዳሙ ማኅበረ ካህናትና ምእመናን ተገኝተዋል።
ከበዓታ ለማርያም ገዳም ቀደም ብላ በ1879 ዓ/ም የተመሠረተችው ደብረ መንክራት ሥዕል ቤት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ስትሆን በኋላም ለአባታቸው ለአጼ ምኒልክ መታሰቢያ እንዲሆን ልጃቸው ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ በ1909 ቦታውን በማስጠረግ በዓመቱም በ1910 ዓ/ም በግብጻዊው ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ቡራኬ ተከናውኖ መሠረት ድንጋይ ተቀመጠ። ከዚያም ከ10 ዓመታት በኋላ ታኅሣሥ 3/በ1920 ዓ/ም በእጨጌ ገብረ መንፈስ ቅዱስ በኋላ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ ቡራኬው ተከናውኖ ታቦቱን ከጎንደር በማስመጣት በክብር እንዳስገቡ ታሪክ ይናገራል።
ቤተ ማርያም ዓለሙ
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ አገልግሎት/Addis Ababa Diocese Media Service
