በሱዳን ካርቱም በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት የተዘጋው ታሪካዊው የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን የሚከፈትበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የተመራው ልዑክ በኢትዮጵያ ከሱዳን አምባሳደር ጋር ተወያዩ፡፡
ነሐሴ 29 ቀን 2018 ዓ.ም
በሰሜን አፍሪካ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የካርቱም ደብረ ሰላም መድኀኔዓለም ቤተክርስቲያን ከ50 ዓመታት በፊት በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ አማካኝነት በካርቱም ከተማ ደረጃ አንድ በሚባል ሥፍራ የታነጸ ታላቅ ቤተክርስቲያን መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በሱዳን በተቀሰቀሰው የእርስ በእርስ ጦርነት ሳቢያ አገልግሎቱ ተቋርጦ የቆየው ይህ ታሪካዊ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን በተጨማሪ ለኤርትራ ኦርቶዶክሳዊያን ዘርፈ ብዙ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በጦርነት ምክንያት ቤተክርስቲያን ተዘግቷል፣ ካህናቱ፣ ምእመናንም ከአካባቢያቸው መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡
የዐቢይ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ አቶ ኢሳያይስ ከተማ “አገልግሎት የምናገኝባት በደስታ፣ በሐዘን፣ በችግራችን ጊዜ የምንጠለልባት የበረሓ ገነት ቤተክርስቲያን ዳግም ተከፍታ አገልግሎት እንድትሰጥ እየሠራን ነው” ብለዋል፡፡ የዐቢይ ኮሚቴው ጸሐፊ አቶ ወሰን ተክለ ማርያም “በሱዳን በርካታ ኢትዮውያንና ኤርትራውያን አገልግሎት የሚያገኙባት ብቸኛ ቤተክርስቲያን መሆኗን ገልጸው፤ ፈለገ ሰላም 1ኛና 2ኛ ደረጃ ት/ቤትና ፍሬ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የሀገረ ስበብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መጋቤ ሃይማኖት አባ አብርሃም ገረመው እንደተናገሩት “በሦስት ዓመት በፊት በጦርነት ምክንያት አገልግሎቱ ያቋረጠውን ቤተክርስቲያን አሁን ካለው አንጻራዊ ሰላም የተነሣ ቤተክርስቲያን ተከፍቶ አገልግሎት እንዲሰጥ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ መሪነት ክቡር ኤልኤዚን ኢብራሂም ሁሴን፤ በኢትዮጵያ የሱዳን አምባሳደርና በአፍሪካ ኅብረት የሱዳን ተወካይ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ በውይይታቸውም ወቅት ለክቡር አምባሳደር በዋናነት በአምስት ጉዳዮች ላይ ጥያቄ ማቅረባቸውን መጋቤ ሃይማኖት አባ አብርሃም ገረመው ገልጸዋል፡፡ እነዚህም፡-
1. ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን የሚጓዝ ይፋዊ የቤተ ክርስቲያን ልዑክ
የደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን ወቅታዊ ሁኔታ በአካል ለመመልከት፣ የደረሰውን ጉዳት ለመገምገም፣ ከሚመለከታቸው የሱዳን መንግሥት ኃላፊዎችና ተቋማት ጋር ለመወያየት ይፋዊ ልዑክ ከኢትዮጵያ መላክ ትፈልጋለች። ስለዚህ ለዚህ ልዑክ የሚያስፈልገውን የቪዛና የጉዞ ሂደት እንዲሁም ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ለመገናኘት የሚያስፈልገውን ትብብር እንጠይቃለን።
2. በሱዳን የሚኖሩ የቤተ ክርስቲያን አባላትን በይፋ መወከል
ቋሚ የቤተክርስቲያን አገልጋዮች ወደ ካርቱም እስኪመለሱ ድረስ፣ በሱዳን የሚኖሩ የቤተ ክርስቲያናችን አባላትን በሀገረ ስብከቱ በይፋ ለመወከል እንፈልጋለን። እነዚህ ተወካዮች የቤተ ክርስቲያኑን ንብረት እንዲጠብቁ፣ ሁኔታውን እንዲገመግሙ፣ አስፈላጊ የጽዳትና የጥገና ሥራዎችን እንዲያስተባብሩ እና በሀገረ ስብከቱ የሚሰጣቸውን ሌሎች ኃላፊነቶች እንዲወጡ እንፈልጋለን። ለዚህ የሚያስፈልገውን ሕጋዊና አስተዳደራዊ ሂደት፣ ፈቃድ፣ ምዝገባ ወይም ሌሎች ሰነዶች በተመለከተ ድጋፍ እንጠይቃለን።
3. የቤተ ክርስቲያኑን ሁኔታ መገምገም፣ መጠበቅ፣ ማጽዳትና መጠገን
የደብረ ሰላም መድኃኔዓለምን ወቅታዊ ሁኔታ በአካል ማየትና መገምገም ትፈልጋለች። ከዚያም በተገኘው ውጤት መሠረት ንብረቱን ከተጨማሪ ጉዳት መጠበቅ፣ ቦታውን ማጽዳት፣ የደረሰውን ጉዳት በፎቶና በቪዲዮ መመዝገብ፣ እንዲሁም አስፈላጊውን የጥገናና የመልሶ ማቋቋም ሥራ ማከናወን ትፈልጋለች።
4. አጠቃላይ የደኅንነት ሁኔታ
ከሁሉም በፊት የሰው ሕይወትና ደኅንነት ዋና ጉዳይ ነው።ስለዚህ በካርቱም ያለውን አጠቃላይ የደኅንነት ሁኔታ፣ በተለይም ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን በሚገኝበት አካባቢ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ይፋዊ ማብራሪያና መመሪያ እንጠይቃለን። በአሁኑ ጊዜ የተፈቀደላቸው የቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ወደ ቦታው መሄድ ደኅንነቱ የተጠበቀና በሕግ የተፈቀደ መሆኑንም ለማወቅ እንፈልጋለን።
5. በቀጣይነት በኤምባሲው በኩል ልናገኘው የምንችለውን ሰው ቢመድቡልን
ቤተ ክርስቲያናችን ዓላማዋ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ሰብዓዊ አገልግሎቷን ብቻ ማስቀጠል ነው። የመጀመሪያው ፍላጎታችን የቤተ ክርስቲያኑን ንብረት መጠበቅ፣ ሁኔታውን በአግባቡ መገምገምና አስፈላጊውን ጥገና ማድረግ ነው። በመቀጠልም የደኅንነትና የሕግ ሁኔታዎች ሲፈቅዱ መንፈሳዊ አገልግሎቱን በደረጃ እንደገና ለመጀመር እንፈልጋለን።
በተጨማሪም ኤምባሲው ከሚመለከታቸው የሱዳን መንግሥት፣ የደኅንነት፣ የካርቱም አስተዳደር፣ የፖሊስና ሌሎች ተገቢ ተቋማት ጋር ግንኙነት እንድንፈጥር እንዲያግዘን በአክብሮት እንጠይቃለን።
በመጨረሻ፣ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለውን ረጅም ታሪካዊ፣ መንፈሳዊ፣ ባህላዊና ሕዝብ-ለሕዝብ ግንኙነት ቤተ ክርስቲያናችን እጅግ ከፍ አድርጋ ትመለከተዋለች።የተጠናቀቀውም አምባሳደሩ በውጭ ጉዳይ በኩል ጥያቄዎቹ በዝርዝር ይምጡልኝ ከዚያም አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ አደርጋለሁ ክቡር አምባሳደሩም ያቀረብናቸውን ጥያቄዎች ተቀብለዋል፤ ተስፋ ሰጪ ውይይት አድርገናል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በውይይት ወቅት ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን ድርጅት የበላይ ኃላፊና የምሥራቅና የሰሜን አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት መልእክት “አምባሳደርም በመጀመሪያ ለዚህ ስብሰባ ጊዜ ሰጥተው ስለተቀበሉን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በሰሜን አፍሪካ የግብፅና የሰሜን ሱዳን ሀገረ ስብከት ስም ያለንን ከፍተኛ ምስጋናና አክብሮት እገልጻለሁ።” ብለዋል፡፡ ብፁዕነታቸው አክለውም “በካርቱም የሚገኘው ደብረ ሰላም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንም ከአምሳ ዓመታት በላይ ለኦርቶዶክስ ምእመናን መንፈሳዊ አገልግሎት፣ እንዲሁም ለሱዳን ሕዝብ ማኅበራዊና ሰብዓዊ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷን ገልጸዋል፡፡ በዚህ ረጅም ዘመን ውስጥ ከሱዳን መንግሥትና ሕዝብ ያገኘነውን ድጋፍና ትብብር ቤተ ክርስቲያናችን በከፍተኛ አክብሮት ታስታውሳለች።
በሱዳን በተከሰተው ግጭት የተነሣ የደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት በጣም አሳዝኖናል። በአሁኑ ጊዜ በሱዳን እየታየ ያለው አንጻራዊ ሰላምና ወደ መረጋጋት የሚደረገው አበረታች እንቅስቃሴ ግን እጅግ ደስ አሰኝቶናል በመላው ሱዳን ሙሉና ዘላቂ ሰላም መረጋጋትና፣ አንድነት እስኪመለስ ድረስ ቤተ ክርስቲያናችን ጸሎቷን ትቀጥላለች።” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም የዐቢይ ኮሚቴው አባላት እንደገለጹት በቀጣይ ጉዳት የደረሰበትን ቤተክርስቲያን ለማደስ፣ አገልግሎቱ እንዲጀመር ለማድረግ ኦርቶዶክሳውያን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡
የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/
