ዝክረ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ
ዜና ሕይወቱ ወዕረፍቱ ለብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ(ከ1928 ዓ/ም – 2007 ዓ/ም)
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቀድሞው አባ ገብረ ማርያም ፈለቀ ከአባታቸው ከአቶ ፈለቀ ለውጤ ከእናታቸው ከወ/ሮ አያልነሽ ሙሉ በወሎ ክፍለ ሀገር በላስታ ቡግና አውራጃ ልዩ ስሙ ሠራብጥ ካህናተ ሰማይ በተባለ ቦታ በ1928 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡
ብፁዕነታቸው በተወለዱበት በካህናተ ሰማይ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ መምሬ ኃይሉ ከሚባሉ መምህር ንባብና ዳዊት፣ ሰዓታትና አምስቱ አእማደ ምሥጢር ተምረዋል፣ በመቀጠልም ወደገነተ ማርያም በመሔድ፤ መሪጌታ ኃይለ ማርያም ከሚባሉ ፀዋትወ ዜማን በደላንታ ወረዳ አርካ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ ከአለቃ ኢሳይያስ ጾመ ድጓን በመማር ላይ እንዳሉ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን በመሔድ ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል የዲቁናን ማዕርግ ተቀበሉ፡፡
በኋላም ወደ ትውልድ ቦታቸው ተመልሰው ጥቂት እንደቆዩ ወደ ደሴ ደ/መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በመሔድ ከመምህር ገብረ እግዚአብሔር መጻሕፍተ ሐዲሳትንና መጽሐፈ መነኰሳትን ተምረዋል።
ከዚህ በኋላ ብፁዕነታቸው በፍፁም ሐሳባቸው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል የመረጡት መንገድ ምንኵስናን በመሆኑ እንደገና ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተመልሰው ምንኵስናን ተቀበሉ፤ በተከታታይም ማዕረገ ቁምስና ከብፁዕ አቡነ ሚካኤል ከተሰጣቸው በኋላ በአከባቢው አጠራር ገዳሚት በትክከለኛ ስሟ ዋልድቢት ቅ/ማርያም አንድነት ገዳም ገብተው ለጥቂት ጊዜ እንዳገለገሉ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከአለቃ በዛብህ ወንድም ጋር ወደ ዞብል ደብረ መድኃኒት አደባባይ ኢየሱስ በመሔድ ከመምህር ወልደ ሰንበት ቅኔ ተምረዋል፡፡
በአዲስ አበባ የወንጌል ትምህርት በማስተማር ሰፊ አገልግሎት ከመስ ጠታቸውም በላይ የመድኃኔ ዓለም በጎ አድራጎት እየተባለ ይጠራ የነበረውን ማኅበር አደራጅተዋል፤ የተማሪዎች አንድነት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን አቋቁመዋል፡፡
ብፁዕ አቡነ ዮሐንስ ሊቀ ጳጳስ ዐቃቤ መንበረ ፓትርያርክ ሆነው ይሠሩ በነበረበት ወቅት በመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ሆነው እንዲሠሩ ተሹመዋል።
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ ለምግባረ ሠናይ የትሩፋት ሥራ ቅድሚያና ትኩረት የሚሰጡ አባት በመሆናቸው በምግባረ ሠናይ የአረጋውያን እናቶችና አባቶች መርጃና መረዳጃ ማኅበርን በማቋቋም በርካታ ችግረኞች እንዲረዱ አድርገዋል።
የአለቃ በዛብህ ወንድም በአሠሩት በሐውልተ ስም መድኃኔ ዓለም ገዳም አለቃው እነደአረፉ ተተክተው ማገልገል ይችሉ ዘንድ በገዳሙ ማኅበር ተመርጠው ለብፁዕ አቡነ ባስልዮስ ቀርበው የገዳሙ
መምህርና አስተዳዳሪ ሆነው እንዲሠሩ ተሰይመዋል።
የማኅደረ ስብሐት ቅድስት ልደታ ለማርያምና ደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ፣ የመናገሻ ገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደሪ፣ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሊቀ ስልጣናት ሆነው አገልግለዋል። የጠቅላይ ቤተ ክህነት መንፈሳዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ፣ የሐረርጌ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው በትጋት አገልግለዋል፤ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ቆይታቸው በአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት የስብከተ ወንጌል እጥረት በነበረበት ቦታ በመዘዋወር የስብከተ ወንጌል አገልግሎት በስፋት እንዲደርስ ከማድረጋቸውም በላይ በአዲስ አበባ በየትምህርት ቤቱ እየተዘዋወሩ ጧት ጧት የግብረ ገብ ትምህርት በማስ ተማር የስብከተ ወንጌል ማኅበራትን በየትምህርት ቤቶቹ እያቋቋሙ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋትና እድገት ከፍተኛ
አስተዋጽኦን አበርክተዋል። ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ በነዚህ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ክብርና አገልግሎት ከተሰየሙ ጀምሮ ባላቸው የሥራ ልምድ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነትና በመልካም አስተዳደር ሲመሩ ቆይተዋል..
ብፁዕነታቸው በአቢዎቱ ዘመን በመላው የኢትዮጵያ ኦ/ተ/ቤተ ክርስቲያን ተወካዮች ጠቋሚነት ለማዕረገ ጵጵስና የታጩ ቢሆንም ብፁዕነታቸው ግን ሥርዓተ አበውን በመከተል እኔ ለዚህ ታላቅ ማዕረግ አልበቃም በማለት ለብዙ ዓመታት ከቆዩ በኋላ “ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር” እንደተባለው ፈቃደ እግዚአብሔር ሲደርስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ስለ ጵጵስና ምርጫ አፈጻጸም የወጣውን መመዘኛ አሟልተው በመገኘታቸው በቁምስና ደረጃ የኢሉባቦር ሀገረ ስብከት እጩ ኤጲስ ቆጶስ ሆነው እንዲያገለግሉ ስለተፈቀደላቸው በ1986 ዓ.ም. ወደ ኢሉባቦር ሄደው የቀድሞው መንበረ ጳጵስና መቱ ከተማ ላይ ሆነው ሥራቸውን ጀመሩ፡፡
በቅዱስ ሲኖዶሱ ውሳኔ መሰረት በአገልግሎት ላይ እንዳሉ ኅዳር 4 ቀን 1987 ዓ.ም. ‹‹ብፁዕ አባ ፊልጶስ ጳጳስ ዘኢሉባቦር›› ተብለው በብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት አንብሮተ እድ ተሾሙ፡፡
ብፁዕነታቸው በመጀመሪያ በቁምስና ደረጃ ወደ ኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሲሄዱ የኢሉባቦር ሀገረ ስብከት መንበረ ጵጵስና ፈርሶ በጅማ ሀገረ ስብከት ሥር እንዲተዳደር ተደርጎ ስለነበረ መንበረ ጵጵስናውን የመደራጀትና የሀገረ ስብከቱን ጽ/ቤት የማቋቋም ሥራ የብፁዕነታቸው ተቀዳሚ ተግባር ሆኖ ቆይቶ ነበር፤ ብፁዕነታቸው የሀገረ ስብከቱን ካህናትና ምእመናንን በማስተባበር ገንዘብ በማሰባሰብ በርካታ የልማት ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡
ከነዚህም መካከል በዘመናዊ ፕላን የተሠራው የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ሕንፃ ተጠቃሽ ነው፡፡
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ ወደ ኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሲመጡ የነበሩት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ብዛት 217 ሲሆኑ በዘመነ ጵጵስናቸው ባደረጉት የማስተባበር ሥራ 93 አብያተ ክርስቲያናት እንዲጨመሩ በማድረግ ብፁዕነታቸው በሞት እስከ ተለዩበት ሰዓት 310 የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሀገረ ስብከቱ ነበሩ፡፡
የአብያተ ክርስቲያናቱ ቁጥር ሊያድግ የቻለው፤ ብፁዕነታቸው በየወረዳው ሐዋርያዊ ጉዞ እያደረጉ ፣ በየመቃብር ቤቱ እያደሩ ስብከተ ወንጌልን በማስፋፋት የፈረሱ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታደሱ፣ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ በማድረግ ታላላቅ ተግባራትን በማከናወናቸው ነው ::
ከዚህ በላይእንደተገለጸው ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ከቁምስና ደረጃ እስከ ማዕርገ ጵጵስና ድረስ በቆዩባቸው ሃያ ሁለት የሥራና የአገልግሎት ዘመናቸው በኢሉባቦር ሀገረ ስብከት አዲስ ተቋቁመው በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ የተመረቁ ጠቅላላ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ብዛት 93 መድረሱ ተረጋግጦአል፡፡
ከዚህም ሌላ በሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና አካባቢ ከሚገኙት አድባራት መካከል የፈለገ ሕይወት ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ከርስቲያን የካህናት ማሠልጠኛ እና የአንድነት ገዳም ሆና እንድታገለግል አድርገዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በጋምቤላ ሀገረ ስብከት ያበረከቱት አገልግሎት
ቅዱስ ሲኖዶስ ግንቦት 22 ቀን 1992 ዓ.ም. ባደረገው ምልዓተ ጉባኤ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ሊቀ ጳጳስ በኢሉባቦር ሀገረ ስብከት ሥራቸው ላይ የጋምቤላ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው ደርበው እንዲሠሩ ተወስኖ ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ በደረሳቸው ደብዳቤ መሠረት ሁለቱን አህጉረ ስብከት አጣምረው በመምራት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ተወጥተዋል፣ የጋምቤላን ሀገረ ስብከት በሊቀ ጵጵስና እንዲመሩ ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡
ከዚህም መካከል ብፁዕ ወቅዱስ ዶ/ር አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖትን በመጋበዝ የከልሉን ብሔረሰብ ከፕሬዚዳንቱ ጀምሮ በማስጠመቅ ወደ ክርስትና ሕይወት እንዲገቡ አድርገዋል፤
ከዚህም ጋር በከልሉ የልማት ሥራዎች እንዲፋጠኑ አድርገዋል ፣ በጎደሬ ወረዳ ከስምንት ያላነሱ አብያተ ክርስቲያናትን አሳንፀዋል። በ1996 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል በተከሰተው የርእስ በርስ ግጭት የልጆቼን ችግር አብሬ መካፈል አለብኝ በማለት ከቦታው ድረስ በመገኘት ሕዝቡን በማጽናናት የማረጋጋቱን ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አከናውነዋል። በቦታውም ዘላቂ ሰላም እስከሚሰፍን ድረስ በማስተባበር የአባትነት ድርሻቸውን በሚገባ ተወጥተዋል፡፡
ብፁዕነታቸው በጠቅላይ ሥራ አስኪያጅነት ያበረከቱት አገልግሎት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሚያዝያ 21 ቀን 2002 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ለሦስት ዓመታት የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው እንዲሠሩ ተደርጓል። በዚህ ከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነታቸው፤ በቤተ ክርስቲያን ተጠግተው በሥራ አጥነት የሚቸገሩትን አቅም በፈቀደ መጠን ሥራ እንዲያገኙ በማድረግና በዝቅተኛ ደመወዝ ምክንያት የኑሮ ጫና የበዛባቸውን ሠራተኞች አስፈላጊውን የደመወዝ ማስተካከያ በማድረግ ከመንበረ ፓትርያርከ የየመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች ጋር በመተባበር የዋና ሥራ አስኪያጅነት ኃላፊነታቸውን ተመስግነው አጠናቀዋል።
በቅዱስ ሲኖዶስ አባልነታቸው በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ወከለው በዓለም አቀፍ ጉባኤያት ላይ ተሳትፈዋል።
ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ “ድንግሊቱን” በሚል አነጋገራቸው የሚታወቁ ሲሆን በሕይወት ዘመናቸው ለሰው የሚራሩ፣ ትሁትና ደግ የትሩፋት አባት እንደነበሩና በርካታ የደሀ ልጆችን በማሳደግ በማስተማር ራሳቸውን ከመርዳት አልፈው ለሀገር፣ ለወገን የሚጠቅሙ ልጆችን በማስተማር ለቁም ነገር አብቅተዋል፡፡ ብፁዕነታቸው በጊዜ ሳይገደቡ ዘወትር የጸሎት መጻሕፍት ከእጃቸው የማይለይ ለጸሎት የተጉና የትሩፋት አባትም ነበሩ።
ብፁዕነታቸው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሀገርና በውጭ ሀገር ሲታከሙ ቆይተው “አፈርነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ” በተባለው አምላካዊ ቃል መሠረት ነሐሴ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በተወለዱ በ79 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
የቀብራቸውም ስነ ሥርዓት፤ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፤ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የመንበረ ፓትርያርክ የየመምሪያና የድርጅት ኃላፊዎች የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የኢሉባቡርና የጋምቤላ አህጉረ ስብከት ተወካዮች ወዳጅ ዘመድ ቤተሰቦቻቸው በተገኙበት ቀደም ሲል ሊቀ ሥልጣናት ተብለው በመሾም በርካታ ማህበራዊ እና መንፈሳዊ አገልግሎት ባበረከቱበት በአዲስ አበባ መንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ነሐሴ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. ተፈጽሟል ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የብፁዕነታቸውን ነፍስ ከቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታት ጋር ይደምርልን፤ አሜን !!!
የብፁዕነታቸው በረከት አይለየን!!
ነሐሴ 25 ቀን 2018 ዓ/ም
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ አገልግሎት/Addis Ababa Diocese Media Service
