የሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በቃሊቲ መካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ ውሏል::
ሐምሌ ፲፱//፳፻፲፰ ዓ/ም የአ/አ/ሀገረ ስብከት ሚዲያየሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ስር በሚገኘው በቃሊቲ መካነ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ቤ/ክ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት በድምቀት ተከብሮ ውሏል!
የደብሩ አስተዳዳሪ መ/ሕ አሽኔ መኮንን ለብፁዕነታቸው፣ለክቡር ዋና ሥራ አስኪያጁና በክብረ በዓሉ ላይ ለተገኙት በሙሉ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ክቡር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ” (ሉቃ 1፥19) የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መነሻ በማድረግ የዕለቱን ትምህርት አስተምረዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን እንደ ቅድስት ኢየሉጣና ቅዱስ ቂርቆስ መንፈሳዊ ሕይወትን ልንኖር ይገባል ሲሉ አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል።
አያይዘውም ልጆች እንደ ቅዱስ ቂርቆስ በመንፈሳዊ ሕይወት ብርቱ ሆነው እዲያድጉ ወላጆች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በአጽንኦት ገልጸዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባና ሀዲያ ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣ ክቡር መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገብረ መድኅን ንጉሤ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ክቡር ሊ/ካ ዕዝራ ንዋይ የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ሊ/ት ደመላሽ ቶጋ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ ዋና ክፍል ኃላፊ፣ የደብሩ አስተዳዳሪ መ/ሕ አሽኔ መኮንን፣የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና እጅግ በርካታ ምእመናን ተገኝተዋል።
መረጃው የክፍለ ከተማው ቤተክህነት ጽ/ቤት ነው
