” የገዳማት ኅብረትና የሚዲያ አጠቃቀም ” በሚል መሪ ሐሳብ የገዳማት ኅብረት ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣የ ራያ ሀገረ ስብከትና የማኅበራት ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ በተገኙበት የግማሽ ቀን ውይይት አካሄደ።
ሐምሌ 11 ቀን 2018 ዓ.ምበመንበረ ፓትርያርክ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የተካሄደው
ውይይት የተጀመረው “ጌታ ሆይ ውሃ የሆነውን ገዳማዊ ሕይወታችንን ወደ ወይን ትቀይረው ዘንድ ከጉባኤያችን ግባ”
በሚል ተማጽኖ ነው።
ጉባኤው በዓመት ሁለት ጊዜ መደበኛ ስብሰባ የሚያካሂድ ሲሆን የአሁኑ ጉባኤ ሁለተኛውና የዓመቱ ማጠቃለያ መሆኑ ተገልጿል።
በጉባኤው መጀመሪያ ላይ የኅብረቱ ሰብሳቢ የሆኑት አባ ዘኢየሱስ ወጋየሁ የምሁር አቡነ ዜና ማርቆስ አንድነት ገዳም አበምኔት ስለሚዲያ አጠቃቀም ለተሰብሳቢው ገለጻ አድርገዋል።
አባ ዘኢየሱስ ወጋየሁ ባደረጉት ገለጻ የገዳም አባቶች በሚዲያ የሚናገሩት መልዕክት የተጠና እንዲሁም ጥንቃቄ የተሞላው መሆን እንዳለበት አብራርተዋል።
ተሰብሳቢ አባቶችም እና እናቶች ቅዱስ ሲኖዶስን በማመስገን ጭምር ተገቢ የሆነ አስተያየት ሰጥተዋል።
በተሰብሳቢ አባቶችና አናቶች በተሰጠው ሐሳብ መሠረት ብፁዓን አባቶች አስፈላጊውን መመሪያ እንዲሰጧቸው ጠይቀዋል።
የኅብረቱ የጸሎት አሳራጊ የሆኑት የሐይቅ አቡነ ኢየሱስ ሞዐ ቅዱስ እስጢፋኖስ አንድነት ገዳም አበምኔት መምህር ፍቅረ ዮሐንስ ገብረ ሕይወት በምናኔ ሕይወት ዙሪያ ሰፋ ያለ ትምህርት ሰጥተዋል። አጠቃላይ የጉባኤውን ሂደት የተመለከተ ቃለጉባኤ ተነቧል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው አባታዊ ተምህርት የሰጡ ሲሆን የቀደሙ አባቶች ረሀቡን ጥሙን እርዛቱን ታግሠው እንደቆዩ አሁንም ትእግስት ለገዳማውያን እና ገዳማውያት ያስፈልጋል ብለዋል።
ገዳማዊ ሕይወታችን በትእግስት ሊጠናከር ይገባናል።
ወደ እግዚአብሔር ጸሎት ማድረስ ለሥራችን መቃናት ይጠቅመናል። የተጣላውን ማስታረቅ ልማትን መሥራት ተገቢ ነው ብለዋል።
እኛም ገዳማትን ማየትና ማጠናከር ይጠበቅብናል በማለት አብራርተዋል። ገዳማት ተደራጅተው በኅብረት መሥራታቸውን ብፁዕነታቸው አድንቀዋል።
ብፁዕነታው አያይዘው እንደገለጹት የውስጥ ችግር መፈታት ያለበት በውስጥ እንጂ በሚዲያ አይደለም። ሚዲያን በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ችግር ፈቺ መሆኑ ቀርቶ የችግር ምንጭ ሊሆን ይችላል ብለዋል።
በመጨረሻም በብፁዕነታቸው ጸሎትና ቡራኬ ስብሰባው ተጠናቋል።
©የኢኦተቤ መገናኛ ብዙኀን አገልግሎት ሥርጭት ድርጅት/ EOTC Broadcasting Service Agency/
