የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በጠቅላይ ቤተ ክህነት እየተገነባ ያለውን ዘመናዊ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የግንባታ ሂደትን ጎበኙ።
ሐምሌ 10 ቀን 2018 ዓ.ም“የሕዝብ ግንኙነት ስኬት ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት” በሚል መሪ ቃል ለአገር ውስጥ የአህጉረ ስብከት የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በተዘጋጀው ስልጠና ካጠናቀቁ በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ግቢ ውስጥ እየተገነባ ያለውን ሁለገብ ዘመናዊ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ የግንባታ ሂደትን ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱ በብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ፤ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ መሪነት የተከናወነ ሲሆን፤ ከብፁዕነታቸው ጋር በመሆን ሠልጣኞቹን ያስጎበኙት ኢንጂነር ሔኖክ ልዑልሰገድ በከፍተኛ ጥራት እየተገነባ ስለሚገኘው ዘመናዊ ዓለም አቀፍ የስብሰባ አዳራሽ ግንባታ ሂደት፣ እንዲሁም ስለ ሕንጻው አጠቃላይ ይዘትና ሁኔታ ዝርዝር ማብራሪያዎችን ለሰልጣኞቹ በሰፊው አቅርበዋል።
ይህ ግዙፍና ዘመናዊ ሕንጻ በአንድ ጊዜ 2,500 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል ትልቅ አዳራሽና ሌሎች መለስተኛ አዳራሾች የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ መሰብሰቢያ አዳራሽ፣ የክብር እንግዶች ማረፊያ፣ ዘመናዊ ምግብ ቤት እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ በርካታ ቢሮዎችን ያካተተ ነው ብለዋል።
ሕንጻው ከመደበኛ የግንባታ ጥበቡ ባሻገር እስከ 30 ቋንቋዎችን በቅጽበት መተርጎም የሚችል የትርጉም ክፍል፣ ዘመናዊ ዲጂታል መጻሕፍት ማከማቻ፣ የጋዜጣዊ መግለጫ መስጫ ክፍል፣ ዘመናዊ የሙቀትና ቅዝቃዜ ማስተካከያ አየር መቆጣጠሪያ እና ደረጃቸውን የጠበቁ የዕይታ ስክሪኖች የተገጠሙለት በመሆኑ የዘመኑ ግብዓቶች የተሟሉለት መሆኑ ተገልጿል።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ለስልጠናው ተሳታፊዎች ባስተላለፉት
አባታዊ ቃለ ምዕዳንና መመሪያ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች በተሠማሩበት አገልግሎት ሁሉ ሳይታክቱና ሳይሰለቹ በርትተው እንዲሠሩና ቤተ ክርስቲያናቸውን በጽናት እንዲያገለግሉ አጥብቀው አሳስበዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ሥራ ዋነኛ ዓላማ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እውነተኛ መልእክት፣ ታሪክና ሥርዓት ለምዕመናን ያለምንም መቆራረጥና ሳይዛባ በትክክል ማድረስ መሆኑን የገለጹት ብፁዕነታቸው፤ ኃላፊዎቹ በዕውቀትና በታማኝነት ተጋድሏቸውን እንዲወጡ አባታዊ መመሪያ ሰጥተዋል።
በመጨረሻም ብፁዕነታቸው ለአህጉረ ስብከቱ የሕዝብ ግንኙነት መሪዎች ለቀጣይ የሥራ ዘመናቸው ስኬትና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚሆን ሰፊ ጸሎትና መንፈሳዊ ቡራኬ በመስጠት መርሐ ግብሩን በታላቅ ክብር አጠናቀዋል።
ዘገባው የኢኦተቤ የሕዝብ ግንኙነት መምሪያ ነው።
ዲ/ን ቅዱስ ጥበቡ
