ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የቦሌ ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያነን የወንዝ አቅጣጫ ማስቀየስና ድልድይ ሥራ ተጠናቆ በብፁዓን አባቶችን ቡራኬ ተመረቀ።
ኢኦተቤ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሚዲያ
ግንቦት ፳/፳፻፲፰ ዓ/ም
ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት የቦሌ ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያነን የወንዝ አቅጣጫ ማስቀየስና ድልድይ ሥራ ተጠናቆ ግንቦት 19/2018 ዓ/ም በብፁዓን አባቶችን ቡራኬ ተመረቀ።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስአበባ የሀዲያ እና ስልጤ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና ብፁዕ አቡነ ናትናኤል የሰሜን አሜሪካ ሚኒሶታ እና ኮሎራዶ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የተሠሡ ሥራዎችንና አሁናዊ የቤተ ክርስቲያኑን ይዞታ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
በመቀጠልም ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበትና 240 ሜትር የሚረዝመውን የወንዝ አቅጣጫ ማስቀየስና የተለያዩ መንደሮችን የሚያገናኘውን ድልድይ ባርከው መርቀዋል።
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ በደብሩ የተሠሩ ሥራዎችን እንዲሁም ከክፍለ ከተማው ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት ጋር በመናበብ የተሠሩ ሥራዎችንን በማድነቅ ለደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብሥራት አብርሃም ዲበኩሉና ማኅበረ ካህናት እንዲሁም ማኅበረ ምእመናን ምስጋና አቅርበዋል።
አክለውም ከመንግሥት ጋር የምንሥራቸው ትውልድ ጠቀምና ቤተ ክርስቲያን ተኮር በተለይም በማኅበረሰባዊ ልማትና ለሰላም ዘብ በመቆም የቤተ ክርስቲያን ክብር በማስጠብቅ መሠረትነት አብረን ልንሠራ ይገባል ብለዋል።
ቀደም ሲል ቦታውን ከ2013 ዓ/ም ጀምሮ እንደሚያውቁት ያስታወሱት ብፁዕ አቡነ ናትናኤል ሊቀ ጳጳስ እጅግ ጠባብ ከነበረበት ቦታና ለአገልግሎትም ምቹነት ከሌሌው ሁኔታ ወጥቶ እንዲህ በሰፊ ቦታ ለማገልገል መብቃት መታደል ነው። በዚህ ላይም መልአከ ብሥራት አብርሃም ዲበኩሉ ወደዚህ ቅዱስ ቦታ በአስተዳዳሪነት ሲመደቡ የሰጠነው ምስክርነት በመልካም ፍሬና ተግባር በመገለጡ የተናጋሪዎችም የሰሚዎችም የጋራ ደስታ ነው ብለዋል።
ከዚሁ ጋር የሚሠራን አካል ማመስገንና ተጨባጭ ሀቅን በዐደባባይ መመስከር መጽሐፋዊ መሆኑን ያስታወሱት ብፁዕነታቸው ከፍተኛ ተግዳሮት ያለበትን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከትን እየመሩ የሚገኙትን ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስን እየሠሩት ስለሚገኙት ሥራዎች በመጥቀስ ምስጋና አቅርበዋል።
የቅዱስ ሲኖዶስ አደራም ሆነ የአባትነት ተግባሩ ዘመኑን የዋጀ፣ የቤተ ክርስቲያንን ክብር የጠበቀ ሁነኛ ለውጥ ማምጣት በመሆኑ ሥራን ብቻ በመሥራት በዝምታና በስክነት መልካም ሥራዎችን እየሠሩ ከሚገኙት ከብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ሊቀ ጳጳስ ጋር ከጎናቸው በመሆኑ ለውጥን ማፍጠንና አደራን መወጣት ለሚለው መርኋቸው ተጨማሪ ጉልበት መሆን ይኖርባችኋል በማለት አሳስበዋል።
የቦሌ ክፍለ ከተማ ሥራ አስፈፃሚ ክቡር አቶ አደፍርስ ሆራ ደብሩ የሠራው የወንዝ ማስቀየስና ድልድይ ሥራ መንግሥት የወንድ ዳርቻ ልማት በሚለው ፕሮጀክቱ ሊሠራው የሚገባው የነበረ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያን ለትውልዳዊ ሥራ ሁልጊዜ ተባባሪ መሆኗን የያየንበት ነው ብለዋል።
አክለውም የወንዝ ዳርቻ ልማት ወንዞችን ወደ ተፈጥሯዊ መልካቸው መመለስን ዓላማ ያደረገ በመሆኑ በቀጣይም በደብሩ የቀሩ ሥራዎችን እንደመንግሥት የሚገባውን ሥራ በመሥራት በተናበበና በተባበረ መልኩ የጋራ ተልእኮን ለማስፈጸም እንደሚጥሩ ቃል ገብተዋል።
መልአከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን የቦሌ ክፍለ ከተማ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ የደብሩ ትናንትና እና ዛሬው ሲታይ በእጅጉ የሚደንቅ መሆኑን ያስታወሱ ሲሆን በዚህ አገልግሎት ቀደም ሲል የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት ክብርት ወ/ሮ ዓለምፀሐይ እንዲሁም አሁን የኃላፊነት ያሉት ሥራ አስፈጻሚ ድርሻቸው ሲፊ ነው ብለዋል።
በኩረ ትጉኀን ጸጋዬ ዓለማየሁ የደብሩ ሰበካ ጉባኤ ምክትል ሊቀመንበር ባቀረቡት ሪፖርት ደብሩ በ2012 ዓ.ም ከተመሠረተ ጀምሮ የተከናወኑ ሥራዎችን ያብራሩ ሲሆን በመልአከ ብሥራት አብርሃም ዲበኩሉ መሪነት የተሠሩ በርካታ ሥራዎችን በመዘርዘር ለአስተዳዳሪው ያላቸውን አክብሮት ከምስጋና ጋር ገልጸዋል።
ደብሩ የሁለት ወንድሞች መስዋዕትነት የተከፈለበት መሆኑን ያስታወሱት ም/ሊቀ መንበሩ ለመታሰቢያቸውንም የተጠናከረ የወንጌል አገልግሎት ጉባኤ በማከናወን መሆኑን ተናግረዋል።
የተሠራው ልማት ሥራ አስፈላጊነትን ሲገልጹ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ቦታ ምቹ ከማድረግ እና በአካባቢው ያሉ ኦርቶዶክሳውያን በወንዙ ምክንያት የሚደርስባቸውን መጠነኛ እግልት በቋሚነት ከመፍታት እንዲሁም ሕጋዊ ይዞታውን ከማስጠበቅ አንጻር ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተጠቁመዋል።
የደብሩ አስተዳዳሪ መልአከ ብሥራት መምህር አብርሃም ዲበኩሉ በበኩላቸው በተከናወነው የልማት ሥራ አስተዋጽኦ ላበረከቱት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል ።
በተለይም የክፍለ ከተማው ቤተ ክህነትና የክፍለ ከተማው የመንግሥት የሥራ ሐላፊዎች እንዲሁም የተለያዩ በጎ አድራጊ ኦርቶዶክሳውያን ላደረጉት ድጋፍና ትብብር በእጅጉ እናመሰግናለን ብለዋል።
በመጨረሻም ደብሩ በሚሠራቸው የልማት ሥራዎች ድርሻቸውን ለተወጡ ኦርቶዶክሳውያን ፣ በጸሎት፣በሐሳብ፣ በጉልበትና በገንዘብ ላገዙ አካላት የእውቅና ምስጋና ሰርተፊኬት እንዲሁም የክብር ካባና የመጽሐፍ ቅዱስ ስጦታ ተብርክቶላቸዋል።
በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ ብፁዓን አባቶች እና የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ መልዓከ ብርሃን ሩፋኤል የማነ ብርሃን ፣ ክቡር አቶ አደፍርስ ሆራ የቦሌ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ መልአከ ስብሐት ዐቢይ ዘለቀ የብፁዕ ሊቀ ጳጳስ ልዩ ጸሐፊ፣ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣
የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ሊቃውንት እንዲሁም በርካታ ምዕመናን ተገኝተዋል።
📷ዲ/ን ቅዱስ ጥበቡ
