የመስቀል ደመራ በዓል አከባበርን አስመልክቶ ሲካሄድ የቆየው የውይይት የማጠቃለያ መድረክ መርሐ ግብር በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ተካሄደ።
መስከረም ፲፪/፳፻፲፱ ዓ/ም የአ/አ/ሀገረ ስብከት ሚዲያ
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላም እና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ፣ ከአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ፣ ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት እና ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጠቅላይ መምሪያ ጋር በመተባበር የ2019 ዓ.ም የደመራ እና የመስቀል በዓል አከባበርን አስመልክቶ ያዘጋጀው የማጠቃለያ መድረክ በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ተካሄዷል።
በመስቀል በዓል አከባበር ዙሪያ በወረዳዎች እና በክፍለ ከተማዎች ሲካሄድ የቆየው የማጠቃለያ ውይይት አካል በሆነው በዚህ መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዳንኤል፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ደኔሮ፣ የአድባራት እና ገዳማት አስተዳዳሪዎች፣ የመስቀል ደመራ ዐብይ ኮሚቴ አባላት እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ መልአከ ብርሃን ሰሎሞን በቀለ፣ የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ ትውፊቱንና ክብሩን በጠበቀ መልኩ በሰላም፣ በደኅንነት እና በድምቀት እንዲከበር ሁሉም የበዓሉ ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሠሩ አሳስበዋል። ሥራ አስኪያጁ እንደገለጹት፣ የመስቀል በዓል በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ በመሆኑ የሀገሪቱን ሰላም፣ አንድነት፣ ልማትና ትብብር ገጽታ ለዓለም ለማሳየት ልዩ አጋጣሚ በመሆኑ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ አማካኝነት የተቋቋሙ የተለያዩ ኮሚቴዎችና አስተባባሪዎች በየድርሻቸው እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የቅዱስ መስቀል ደመራ በዓል ከሃይማኖታዊ ዕሴቱ ባሻገር የፍቅር፣ አንድነትና መተባበር ታላቅ ተምሳሌት በመሆን የሕዝባችንን አብሮነት፣ ሰላም እና መቻቻል የሚያጠናክር በዩኔስኮ እውቅና የተሰጠው ዓለም አቀፍ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል መሆኑን ጠቅሰዋል። ንግሥት እሌኒ እውነተኛውን መስቀል ለማግኘት ብዙ ውጣ ውረዶችንና ፈተናዎችን አልፋ የልብ ፍላጎቷ እንደተሳካላት ሁሉ፣ እኛም ሁላችንም በአንድ ልብና ድምጽ በመተባበር የሰላምና የፍቅር እሴቶችን በማስቀጠል የበዓሉን በረከት እና ታላቅነት በጋራ ማሳየት እንደሚገባን አሳስበዋል።
በተጨማሪም የክፍላተ ከተማ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጆች የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች እና የቤተክርስቲያን አስተባባሪዎች በየአካባቢያቸው ጉዳዮችን በቅርበት በመከታተል የበዓሉን ሰላማዊ አከባበር ሊያደናቅፉ የሚችሉ ጉዳዮችን በቅድሚያ እንዲፈቱ ጠይቀዋል።
ረጅም ታሪካዊና ማኅበራዊ እሴት ያለው፣ በታላቅ ድምቀት የሚከበር መንፈሳዊና ባሕላዊ በዓል እንዲሁም በመላው ዓለም በድምቀት የሚከበርና ብዙ ሕዝብ የሚሳተፍበት በዓል በመሆኑ፣ የበዓሉን ድምቀት ሊያደበዝዙ የሚችሉ ጉዳዮችን በመለየት ተገቢና የጋራ መፍትሔ እንዲዘጋጅላቸው ለማድረግ የተዘጋጀ መድረክ መሆኑን የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ መጋቢ ተአምራት አበጋዝ ገልጸዋል።
በመንፈሳዊ በዓላት ዙሪያ የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት ረዳት ፕሮፌሰር ቀሲስ ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ መንፈሳዊ በዓላት እግዚአብሔርን የምናከብርባቸው፣ የሰላም፣ የፍቅርና የአንድነት መገለጫዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። በዓላት የሰው ልጆች የፈጠሯቸው ሥርዓቶች ሳይሆኑ፣ በእምነት ሥርዓት መሠረት እግዚአብሔር ያዘዘውን ለመዘከርና ለማክበር የሚደረጉ እንዲሁም በክርስትና ቀኖናና ሥርዓት የሚከበሩ ሥርዐተ አምልኮ እንጂ ለሥጋዊ ለደማዊ ሐሳቦች ማስፈጸሚያ የሚደረጉ አለመሆናቸውን አብራርተዋል። አማኞች በአንድነት ተሰብስበው እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑበት፣ እምነታቸውን የሚያጠናክሩበትና ለትውልድ እሴቶችን የሚያስተላልፉበት አጋጣሚዎች እንደሆኑም አስታውሰዋል። በተለይ የመስቀል በዓል ጥልና ልዩነት ተወግዶ አንድነትና ሰላም የተገለጠበት፣ የሞት ምልክት የነበረው መስቀል የሕይወትና የድኅነት ምልክት የሆነበትን ታሪክ የሚታሰብበት፣ እንዲሁም የሃይማኖት ነጻነትና የእኩልነት መልእክት የያዘ በዓል መሆኑን አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ዳንኤል በበኩላቸው፣ በዓሉ ለኢትዮጵያውያን ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ሲሆን ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባሻገር ትልቅ ባህላዊ እሴት ያለውና ብዙ ምዕመናንን በዐደባባይ የሚያሰባስብ በመሆኑ የበዓሉ ሥርዓት እንዳይዛባና ከሃይማኖታዊ ትውፊቱ ውጪ የሆኑ ተግባራት እንዳይፈጸሙ የሃይማኖት መሪዎች፣ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎችና የመንግሥት አካላት በጋራ መምከርና መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል። በዓሉን አጋጣሚ በማድረግ ሁከት ወይም ሌላ ችግር ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎች እንዳይሳኩ በየደመራ ስፍራው ምዕመናንን በመምከርና በማስተማር በዓሉ በሰላምና በሥርዓት እንዲከወን ሁሉም አካል የበኩሉን ኃላፊነት እንዲወጣ አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል አስራት ደኔሮ በበኩላቸው በመልእክታቸው፣ የመስቀል በዓል ሃይማኖታዊ እሴቱን ጠብቆ እንዲከበርና ከዚህ በፊት የማይፈለጉና የሚወገዙ ተግባራት በበዓሉ ላይ እንዳይታዩ የየቤተክርስቲያኑ ኃላፊዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸው ኃላፊነት ከፍተኛ መሆኑን አሳስበዋል። አክለውም ምዕመኑ አላስፈላጊ ነገሮችን ሲመለከት ጥቆማ እንዲያደርግ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ ሁሉም አካላት ኃላፊነታቸውን በጥልቀት በመገንዘብ ከዚህ በፊት ከነበረው ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
ዘጋቢ ጽናት አስቻለው
