ቤተ ክርስቲያናችን የራሷ የሆነ የዳበረ የቀኖና፣ የፍትሕና የአስተዳደር ሥርዓት ያላት በመሆኑ፣ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤቷ ሙሉ ዕውቅናና የሕግ ከለላ አግኝቶ ቢደራጅ በርካታ አገራዊ ጥቅሞችን ያስገኛል:: ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ አቡነ ሳዊሮስ
የቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ፍርድ ቤት እንደገና ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ የውይይት መርሐ ግብር ላይ ያስተላላፉት መክፈቻ መልእክት አስተላላፈዋል።ሙሉ መልእክታቸው እንደሚከተለው ተቀምጧል።
ክቡራንና ክቡራት፣
ክቡራት፣ የዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ተሳታፊዎችና ጥሪ የተደረገላችሁ የክብር እንግዶች፤ በመጀመሪያ፣ የሀገራችንን የፍትሕ ሥርዓት መሠረትና የወደፊት አቅጣጫ ለመቃኘት በተዘጋጀው በዚህ ታላቅ መድረክ ላይ፣ በመገኘታችን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ።
ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረና የዳበረ የመንግሥትነት ታሪክ፣ የማኅበራዊ መስተጋብርና የሕግ ሥርዓት ባለቤት እንድትሆን ካደረጓት ዋነኛ ምሰሶዎች መካከል አንዷና ግንባር ቀደሟ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት::
ቤተ ክርስቲያናችን ለዘመናት የሃይማኖት ተቋም ብቻ ሳትሆን፣ የፍትሕ፣ የዕርቅ፣ የሕግና ሥርዓት ዋነኛ ምንጭ ሆና ስታገለግል ኖራለች:: እንደዛሬው ባሉ ታሪካዊ አጋጣሚዎች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለሀገራችን የፍትሕ ሥርዓት ያበረከተችውን ታሪካዊ አስተዋጽኦ፣ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶቻችን በመንግሥት ሕጋዊ ዕውቅና አግኝተው ቢደራጁ ሊያበረክቱ የሚችሉትን ሁለንተናዊ ጠቀሜታ፣ እና እስካሁን ይህ ዕውቅና ባለመገኘቱ ምክንያት እየተፈጠሩ ያሉትን ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸውን በስፋት መዳሰስ ጠቃሚ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የሕግ ታሪክ ሲጠና፣ የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክና ሥነ- ጽሑፍ ሳይዳሰስ ፍጹም ሙሉ ሊሆን አይችልም᎓᎓ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሀገሪቱ የፍትሕ ሥርዓት ግንባታ ላይ ያበረከተችው አስተዋጽኦ በብዙ ዘርፎች የሚገለጽ ነው፡፡
ለዘመናት የኢትዮጵያ የፍትሐ ብሔርና የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሠረት ሆኖ ያገለገለው ፍትሐ ነገሥት፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ተተርጉሞ፣ ተብራርቶና ተጠብቆ የቆየ የሕግ ሰነድ ነው፡፡
ፍትሐ ነገሥት መንፈሳዊ ድንጋጌዎችን ብቻ ሳይሆን የንብረት፣ የውርስ፣ የጋብቻ፣ የውልና የቅጣት ሕጎችን ሁሉ በስፋት የያዘ በመሆኑ፣ ለዘመናዊው የኢትዮጵያ ሕግጋት እንደ ትልቅ መነሻና ምንጭ ሆኖ አገልግሏል። ከዚህም ባሻገር ማኅበረሰቡ በሰላምና በፍትሕ እንዲኖር፣ መደበኛ ፍርድ ቤቶች ከመቋቋማቸው በፊትና በኋላ፣ ቤተ ክርስቲያን በየሰበካው ባሏት መዋቅሮች አማካኝነት የዕርቅና የሽምግልና ሥርዓትን ስትመራ ቆይታለች።
የንስሐ አባቶች፣ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎች ማኅበራዊ ግጭቶችን፣ የቤተሰብ መፍረስንና የድንበር ክርክሮችን በይቅርታና በፍትሕ በመፍታት፣ ማኅበረሰባዊ መረጋጋትን አስጠብቀዋል።
በተለይም ቤተ ክርስቲያን ነገሥታቱ ሳይቀሩ በሕግና በሥርዓት እንዲመሩ፣ ፍትሕ እንዳያጓድሉና የደካሞችን መብት እንዳይረግጡ በሐዋርያዊ ቃል ስትገሥጽና ስታቀና መኖሯ፣ በሕዝቡ ዘንድ ለሕግ መገዛትንና የፈጣሪን ፍርሃት በመቅረጽ፣ ወንጀል እንዳይስፋፋ ትልቅ የቅድመ-መከላከል ሥራ እንድታከናውን አስችሏታል።
ይህንን ታሪካዊ መሠረት ይዘን ወደ ዛሬው እውነታ ስንመጣ፣ በአሁኑ ወቅት በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ መሠረት (፴፬(፭) በሃይማኖትና በባሕል ሕጎች ላይ ተመሥርተው የሚዳኙ የሃይማኖትና የባሕል ፍርድ ቤቶች ዕውቅና ሊያገኙ እንደሚችሉ በግልጽ ተደንግጓል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነ የዳበረ የቀኖና፣ የፍትሕና የአስተዳደር ሥርዓት ያላት በመሆኑ፣ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤቷ ሙሉ ዕውቅናና የሕግ ከለላ አግኝቶ ቢደራጅ በርካታ አገራዊ ጥቅሞችን ያስገኛል::
በመጀመሪያ ደረጃ፣ በአሁኑ ወቅት በመደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚስተዋለውን የክስ መከማቸትና የውሳኔ መዘግየት በእጅጉ ለመቀነስ ይረዳል። ከመንፈሳዊ ሥርዓት፣ ከውርስ፣ ከትዳርና ከሰበካ አስተዳደር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በመንፈሳዊ ፍርድ ቤት ቢታዩ፣ መደበኛ ፍርድ ቤቶች በሌሎች ከባድ የወንጀልና የንግድ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ሰፊ ዕድል ይሰጣል።
በተጨማሪም፣ ከሃይማኖትና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ቀኖና ጋር የተያያዙ ውስብስብ ክርክሮች በመደበኛ ሕግ ብቻ ለመወሰን አስቸጋሪ በመሆናቸው፣ እነዚህን ጉዳዮች የቤተ ክርስቲያንን ሕግ በሚያውቁ የሃይማኖት ሊቃውንትና የሕግ ባለሙያዎች መዳኘት ይበልጥ ፍትሐዊና ተቀባይነት ያለው ውሳኔ ያስገኛል።
ይህ አሠራር የመንግሥትንና የሃይማኖትን መለያየት መርሕ ይበልጥ በማጠናከር፣ መደበኛ ፍርድ ቤቶች በሃይማኖት ውስጥ ካሉ የአስተዳደርና የቀኖና ክርክሮች የጊዜና የሰው ኃይል ጫና እንዲርቁ፣ ቤተ ክርስቲያንም በራሷ ሕግ ራሷን እንድታስተዳድር በማድረግ ተቋማዊ ነጻነቷን ያረጋግጣል።
የመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች ዓላማ ቅጣት ላይ ብቻ ያተኮረ አይደለም፡፡
ይልቁንም ሰላምን፣ ንስሐንና ዕርቅን መሠረት ያደረገ በመሆኑ፣ በማኅበረሰቡ መካከል ጠላትነት እንዳይሰፍንና ፍቅር እንዲመሠረት የማድረጉ ሚና የጎላ ነው።
ይሁን እንጂ፣ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤታችን ይህ ሕገ-መንግሥታዊ ዕውቅና ሳያገኝና አዋጅ ሳይወጣለት በመቆየቱ ምክንያት፣ ባለፉት ዓመታት ተቋማዊና ሀገራዊ የሆኑ በርካታ ችግሮች ተከስተዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያን በቀኖናዋ መሠረት የምታሳልፋቸው መንፈሳዊ ውሳኔዎች፣ ለምሳሌ የክህነት እገዳና የቅጣት ውሳኔዎች፣ ሕጋዊ ዕውቅና የሌለው አሠራር ተደርገው በመቆጠራቸው፣ ግለሰቦች ጉዳዩን ወደ መደበኛ ፍርድ ቤት በመውሰድ መንፈሳዊውን ውሳኔ የሚያሽሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
ይህ አሠራር የቤተ ክርስቲያንን ክብርና ልዕልና የሚነካ ከመሆኑም በላይ፣ መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶቻችን በመንግሥት ዘንድ የሕግ ከለላና ዕውቅና ስለሌላቸው፣ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች በሲቪል መዋቅሩ ተፈጻሚነት እንዲያጡ አድርጓቸዋል።
ይህ ደግሞ ሥርዓት አልበኝነትን የሚያበረታታና የተቋሙን አስተዳደራዊ መዋቅር የሚያዳክም ሆኖ ቆይቷል።
በቤተ ክርስቲያን የውስጥ አሠራርና በመንፈሳዊ ፍርድ ቤት በቀላሉ ሊያልቁ የሚችሉ አነስተኛ የንብረት፣ የውርስና የአስተዳደር ክርክሮች መደበኛ ፍርድ ቤቶችን በማጨናነቅ፣ የፍትሕ መዘግየትን አስከትለዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ሕጋዊ ማዕቀፍ ባለመኖሩ፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስም የሚነግዱ፣ የውስጥ መዋቅርን የሚፈታተኑና የንብረት ምዝበራ የሚፈጽሙ አካላት ቤት ሊቀጡ ሲገባቸው፣ በሕግ ክፍተት ምክንያት ተጠያቂ ሳይሆኑ የሚቀሩበትና በምትኩ ተቋሙ ለከፍተኛ ኪሣራና መከፋፈል የሚዳረግበት ሁኔታ ተከስቷል።
ለቤተ በመንፈሳዊ ፍርድ ክቡራንና ክቡራት፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ፍርድ ቤት በሕግ ታውቆና ተደራጅቶ መሥራት መጀመር፣ ክርስቲያኒቱ ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን የፍትሕ ሥርዓት መዘመንና መቃናት ትልቅ አስተዋጽኦ አለው። ይህ ጉዳይ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ፣ በሕገ-መንግሥቱ በተቀመጠው መብት መሠረት ሊተገበር ይገባል። ስለሆነም፣ ይህ ታላቅ ጉባኤ የሕግ መወሰኛና አስፈጻሚ አካላት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች የሚቋቋሙበትንና የሚመሩበትን ዝርዝር አዋጅና መመሪያ እንዲያጸድቁ አብሮ መሥራት አስፈላጊ ነው::
በመደበኛ ፍርድ ቤቶችና በመንፈሳዊ ፍርድ ቤቶች መካከል ያለውን የሥልጣን ወሰን በግልጽ በመለየት፣ አንዱ ሌላውን የሚያግዝበትና የሚያከብርበት ሥርዓት መዘርጋት ይኖርበታል። ቤተ ክርስቲያናችንም የተሰጣትን ዕውቅና ተጠቅማ፣ ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የሕግና የቀኖና ሊቃውንትን ያቀፉ የመንፈሳዊ ፍርድ ቤት መዋቅሮችን እስከ ታችኛው የሰበካ ደረጃ ድረስ በብቃት የማደራጀት የቤት ሥራዋን ትወጣለች። በመጨረሻም፣ ፍትሕ የሀገር መሠረት፣ ሰላም ደግሞ የልማት ምንጭ በመሆናቸው፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ለዘመናት ያበረከተችውን ታሪካዊ የፍትሕ አቅራቢነት ሚና ዛሬም በተደራጀ መልክ እንድትወጣ የቤተ ክርስቲያን ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ እንዲያገኝና በዐዋጁ መጽደቅ የፍትሕ ሥርዓቷን በራሷ እንድታስቀጥል ታሪካዊ ሁላችሁም የበኩላችሁን እንድታደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ።
ልዑል እግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿንን ይባርክ ይቀድስ!
አባ ሳዊሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
ሰኔ 20 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ
